ውድ ጓደኞቼ፣
በስራ ባልደረቦቼ እገዛ ለመጪው አመት የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ሆኜ ለማገልገል መታጨቴን የምቀበለው በታላቅ አክብሮት ነው። ይህንን ሃላፊነት መወጣት በምጀምርበት በዚህ ወቅት በአለፈው አመት በጋራ ጥረት ያስመዘገብናቸውን ክንውኖች በማሰብ እና በዚህ ባመጣነው መሻሻል ላይ በመመስረት እና በማዳበር ለወደፊቱ የምናስመዘግበውን የተሻለ ውጤት በጉጉት በመጠባበቅ ነው።
ምክር ቤቱ የማህበረሰቡን ዘርፈ ብዙና አጣዳፊ ፍላጎቶች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማሟላት ሲሰራ የቆየ ሲሆን በጣም አስፈላጊ ለሆኑ የማህበራዊ እና የጤና አገልግሎቶች ተጨማሪ በጀት/ገንዘብ/ በመመደብ፣ ለህዝብ ትምህርት ቤቶቻችን ከዚህ በፊቱ በላቀ ደረጃ የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብ፣ በተጠናከረ መልኩ የተከራዮችን ህልውና በማስጠበቅ፣ እንዲሁም አጣዳፊ የሆነውን አቅምን ያገናዛበ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። አዳዲስ የንግድ ተቋማት ወደካውንቲያችን እንዲመጡ ማባረታታት/ለመሳብ እንዲሁም በስራ ላይ ያሉትንም ለመደገፍ የምናደርገውን ጥረት ቀጥለንበታል። ከሞንትጎመሪ ካውንቲ ፖሊስ ጋር በቅንጅት በመስራት እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በተሻለ ሁኔታ በመጠቀም የማህበረሰቦቻችንን ደህንነት በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ እየሰራን እንገኛለን።
በእርግጥ ወደፊት አለጥርጥር አንዳንድ ተግዳሮቶች ሊገጥሙን እንደሚችሉ ብናውቅም ለጋራ እሴቶቻችንን እና አላማዎቻችንን መሳካት በቅንነት እና በአንድነት በመስራት ማናቸውንም ችግሮች መወጣት እንደምንችልና ሞንትጎመሪ ካውንቲያችንንም በተሳካ መልኩ ወደፊት እንደምናራምድ ከልብ አምናለሁ። በዚህ መልኩ ነው ባለፉት ጥቂት አመታት የተጋረጡብን ችግሮችም ስንፈታና ስናሸንፍ የኖርነው። በመሆኑም እስካሁን ስናደርግ እንደነበረው የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሙንም እየተወጣናቸው ውጤታማ በመሆን እንቀጥላለን። እጅጌያችንን ሰብስበን ለስራ በመዘጋጀትና አብረን በመስራት ለጋራ ብልጽና እንድንተጋ ጥሪ አቀርባለሁ።
ምንም አይነት ጥያቄ ካላችሁ ወይንም እገዛ ከፈለጋችሁ ወደኋላ አትበሉ፤ እንደተለመደው ወደቢሮዬ መምጣት/ ማግኘትና መነጋገር ይቻላል።
ከማክበር ሰላምታ ጋር፣
የካውንስሉ ፕሬዚደንት ኬት ስቴዋርት
በፈደራል መንግስት ደረጃ በቅርቡ ሊደረጉ ከታሰቡ ለውጦች ምክንያት የኛ ማህበረሰቦች በልዩ ሁኔታ ተጽእኖ ሊደርስባቸው እንደሚችል እናውቃለን። በዚህም ምክንያት በአካባቢ ደረጃ ሁሉም ሰው ደህንነት እና ቅቡልነት እንዲሰማው እንዲሁም ሁሉም ነዋሪዎች በጣም ጠቃሚ የሆኑ የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን የተመለከተ መረጃ እንዲያገኙ ለማስቻል በሚል ጸንተን እየሰራን እንገኛለን።
የካውንቲው የምክር ቤት አባላት እና የካውንቲው ዋና የስራ አስፈጻሚ በሚገኙበት፤ እሁድ ቀን በዲሴምበር/ታህሳስ 8 ከሰአት ከ 1 እስከ 4 ፒ.ኤም ሮክቪል በሚገኘው የኤግዘኪዩቲቭ ኦፊስ ህንጻ በተዘጋጀው ‘ማህበረሰባችንን ለማገልገል እና ለማገዝ እንተባበር’ / United in Service and Support Community Resource Fair/ በተባለው የመረጃ አውደ ርእይ /ኤግዚቢሽን/ ላይ ሁላችሁም የማህበረሰባችን አባላት እንድትካፈሉ እንጋብዛለን። በዝግጅቱ ላይ ለካውንቲው ነዋሪዎች የሚጠቅሙ ዘርፈ ብዙ የሆኑ መረጃዎች እና የተለያዩ እገዛዎችን ለማግኘት የሚረዱ የሃብት ምንጮች የሚቀርቡ ሲሆን ወደዝግጅቱ ለመጓጓዝ ነጻ የሆነ የራይድ ኦን አውቶቡስ አገልግሎትም ተዘጋጅቷል። Montgomery County website የሚለውን የሞንትጎመሪ ካውንቲ ድረገጽ በመጫን ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይቻላል።
በተጨማሪም እኔ በግሌ “የጉዳት ሰለባዎችንና የስደተኛ ማህበረሰብ አባላትን ደህንነት የማጠናከር ህግ (ዩ ቪዛ ህግ)” የተባለውንና የከባድ ወንጀል ሰለባዎች የዩ ቪዛ አሰራር ሂደትን በመጠቀም ህጋዊ ጥበቃን ለማግኘት እንዳይችሉ እንቅፋት የሚሆኑ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ በማሰብ በቅርቡ በስራ ባልደረቦቼ ለምክር ቤት የቀረበውን የዚህን ህግ ስፖንሰር/ደጋፊ መሆኔን ስገልጽ ኩራት ይሰማኛል። ይህ ህግ የስደተኝነት ወይንም ኢሚግሬሽን ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ያለምንም አድልዎ ሁሉንም የጉዳት ሰለባዎች ማገዝ እና መጠበቅ የሚለውን የሞንትጎመሪ ካውንቲ ጽኑ አቋም የሚያግዝ ህግ ነው። ለተጨማሪ መረጃ ይህን Learn more ይጫኑ።
በአሁኑ ጊዜ በኖርዝ በተዝዳ እና አካባቢው የሚታዩ የተለያዩ ደስ የሚያሰኙ እና አበረታች እንቅስቃሴዎች ስፍራው በፊትም የነበረውን ለኑሮ፣ ለስራ አና ለመዝናኛ ምቹ የመሆን ዝና ከማጠናከራቸውም በይበልጥ እያደገ ያለ እና አሻጋሪ እየሆነ የመጣ ማእከል መሆኑ በግልጽ እየታየ መጥቷል። በ 2026 ለጠናቀቅ ለታሰበውና 163 ከፍተኛ ጥራት ያላቸው፣ ለአካባዊ የአየር ጥራት ተስማሚ የሆኑ እና አቅምን ያገናዘቡ የኪራይ ዩኒቶችን ያቀፈው ዘ ቻይምስ The Chimes የተባለውን በሞንትጎመሪ የመኖሪያ ቤት ሽርክና /ፓርትነርሺፕ/ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ ፈርቀዳጅ ኩነት ላይ የመካፈል አስደሳች አጋጣሚም አግኝቼ ነበር። በዚህ የበልግ ወቅትም ስትራስመስ ስኩዌር /Strathmore Square/ በተባለው ቦታ በፋይፍ ስኩዌርስ ዴቨሎፕመንት፣ በስትራትሞር የሙዙቃ ማእከል፣ በሜትሮ፣ በአማዞን የመኖሪያ ቤት ኤኩቲ ፈንድ እና በሞንትጎመሪ ካውንቲ ሽርክና አማካኝነት እየተገነባ ባለው ልዩ እና ስነጥበብ ተኮር በሆነው መንደር ላይ ከታቀዱት ሁለት የመኖሪያ ቤት ግምባታ ፕሮጀችቶች መካከል የመጀመሪያውን ፕሮጀችት ሪበን ቆርጠን አስጀምረናል።
በኖርዝ በተዝዳ ተጨማሪ ለተሰባጠረ አገልግሎት እና የተለያየ የገቢ አቅም ላላቸው የሚውሉ መኖሪያ ቤቶችን እየገነባን ባለንበት ባሁኑ ወቅት በኖርዝ በተስዳ ከሚገኘው እና ሁለተኛ አመቱን ካስቆጠረው የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ የጤና መረጃ ማስላት ኢንስቲቲዩት /Institute for Health Computing/ ጋር እየተፈጠረ ያለውን አብሮ የመስራት፣ የምርምር እና የፈጠራ ትብብርም ሳላደንቅ አላልፍም። በጣም ዘመናዊ የሆነው የምርምር ስራቸው ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውን ግለሰቦች ወደ ሞንትጎመሪ ካውንቲ እንዲመጡ በማድረጉም ከዛም አልፎ በአጠቃላይ ለአለም ህዝቦች ጤና አጠባበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። የጤና ሳይንስ የወደፊት እጣ በዚሁ በሰሜን በተዝዳ እየተቀረጸ ይገኛል!
በሞንትጎመሪ ኮሞቴ አመታዊ የቁርስ ግብዣ ላይ ተገኝቼ በጣም ድንቅ ጊዜ አሳልፌያለሁ። ይህ ልዩ ክስተት በሞንትጎመሪ ካውንቲ የሚገኙ የበጎ አድራጎት፣ የእምነት፣ የንግድ ባለቤቶች እና በህዝብ የተመረጡ ሃላፊዎች በአንድ ላይ እንዲሰሩ እያደረገ ከመሆኑም በላይ በካውንቲው ውስጥ የሚገኙ እጅግ ድንቅ የሆኑ ድርጅቶች እንዴት በመቀናጀት የተለያዩ የማህበረሰብ አባላትን ለማገልገልና ለማገዝ እንደሚሰሩ ጉልህ ማሳያ ነው። ከሞንትጎመሪ ኮለጅ ሰራተኞች ጋርም አብሬ ተቀምጬ የተወያየሁ ሲሆን በተለይም ከዶክተር ዊሊያምስ ጋር ወቅታዊ መረጃን ለመለዋወጥ እና በኮሌጁ ውስጥ እየተሰሩ ያለ ታላቅ ነገሮችንም ለማወቅ ችያለሁ።
ከታንክስጊቪንግ አውደአመት ቀደም ብሎ በተካሄደ ለአመታዊው የታንክስጊቪንግ የምግብ እደላ የሚሆኑ የምግብ ከረጢቶችን በማዘጋጀት ስራ ላይ ከግሬተር ዋሺንግተን የአድቬንቲስት የማህበረሰብ አገልግሎት የበጎ ፈቃደኞች ጋር አብሬ ተሳትፌ ነበር። ብዙ ጓደኞቼ እና የማህበረሰብ በጎ ፈቃደኞች እንዲህ ባለው ሁኔታ ጊዜያቸውን እና አቅማቸውን ሰውተው አብረው በመስራት በጣም ችግረኛ የሆኑ የማህበረሰብ አባላትን ለመርዳት ሲሰሩ ማየት ሁል ጊዜም ቢሆን በጣም ጥሩ ስሜትን ይፈጥራል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት በራሱ ለጤና የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ያውቁ ኖሯል? በሌሎች ሰዎች ህይወት ላይ ከሚኖረው በጎ አስተዋጽኦ በተጨማሪ የበጎ ፈቃድ መስጠት የርስዎን አእምሮአዊ እና አካላዊ ጤንነት ለማሻሻል ሊረዳ ይችላል/ volunteering can improve your mental and physical health!/። በዚህ የበአል ወቅት ለተለያዩ አካባቢያችን ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የበኩላችሁን ጉልህ ድርሻ መወጣት ትችላላችሁ። የሞንትጎመሪ ካውንቲ የበጎ አገልግሎት መስጫ ማእከል/ Montgomery County Volunteer Center የሚለውን ይህን ማስፈንጠሪያ በመጫን በዚህ ወቅት ያሉ እና ለርስዎ የሚመቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጫ እድሎችን ማግኘት ይችላሉ።