Skip to main content

Council Spotlight

Keeping Up With Kate - Dec. 18, 2024 (Amharic/አማርኛ)

Keeping Up With Kate - Amharic Language Newsletter Banner

ውድ ጓደኖቼ

ይህ የበዓል ወቅት የተለያዩ ነገሮችን መለስ ብለን በጥሞና የምናሰላስልበት እና ምስጋናም የምናቀርብበት አጋጣሚ ነው። የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ሆኜ ስራዬን በምጀምርበት በዚህ ሰዓት በተለይ በዚህ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያቀፈ እና በንቃት እየተንቀሳቀሰ ባለ ማህበረሰብ ውስጥ ለማገልገል በመቻሌ ልባዊ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ።  በሞንትጎመሪ ካውንቲ ማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ ሁሉም ነዋሪዎች በሙሉ የደህንነት ስሜት መኖር፤ መስራት፤ ትምህርት ቤት መሄድ እንዲሁም ማምለክ መቻል አለባቸው። አዲሱን አመት ልንቀበል በተቃረብንበት በዚህ ጊዜም በማናቸውም መልኩ የሚከሰት ጥላቻን ለመዋጋት አሁንም ቁርጠኝታችንን ማረጋገጥና የሚገጥመንም ፈተና ለመጋፈጥ በጋራ መቆም ይገባናል።  በዚህም አጋጣሚ የተቸገሩ ወገኖቻችንን ለመርዳት ርህራሄን በተላበሰ መልኩ ግምባር ቀደም በመሆን የሚጥሩ ነዋሪዎቻችንንም ለማድነቅ እወዳለሁ። በተለይ በአካባቢያችሁ ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የምታሳዩት ድጋፍ፣ ተሳትፎ  እንዲሁም በግልጽ የመወያየት ባህል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ለመግለጽ እወዳለሁ። ከሁላችሁም ጋር ስናደርገው የነበረውን በቅንጅት የመስራት ሁኔታ በመቀጠል በ2025ትም እንዲሁ በጋራ አብረን እንደምንሰራ በጉጉት እጠብቃለሁ።   

መልካም በዓል እንድታሳልፉ፣ እንዲሁም አዲሱ አመት የሰላም እና የደስታ ጊዜ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ!

ምንም አይነት ጥያቄ ካላችሁ ወይንም እገዛ ከፈለጋችሁ ወደኋላ አትበሉ፤ እንደተለመደው ወደቢሮዬ መምጣት/ ማግኘትና መነጋገር ይቻላል።  

ከማክበር ሰላምታ ጋር 

ኬት ስቴዋርት

የካውንስሉ ፕሬዚደንት

በተጨማሪ፣ በሞንትጎመሪ ካውንቲ የእሳት እና ከአደጋ የማዳን አገልግሎት ክፍል አማካኝነት የተዘጋጁ እና በበአል ወቅት ደህንነታችንን ለማስጠበቅ የሚረዱ ሃሳቦችን ለማግኘት  - celebrate the holidays safely with fire safety tips – የሚለውን ድረገጽ ይጎብኙ።

‘ማህበረሰባችንን ለማገልገል እና ለማገዝ እንተባበር’ የመረጃ አውደ ርእይ /ኤግዚቢሽን/

‘ማህበረሰባችንን ለማገልገል እና ለማገዝ እንተባበር’ በተባለው የመረጃ አውደ ርእይ ላይ ለተሳተፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምስጋና እናቀርባለን። በፈዴራል ደረጃ በቅርቡ ለሚፈጸመው የመንግስት ለውጥ በምንዘጋጅበት በአሁኑ ወቅት ዋና ተቀዳሚ ተግባራችን የሚሆነው ለነዋሪዎቻችን በጽናት መቆምና እንግዳ ተቀባይ እና አካታች የሆነ ማህበረሰባዊ ባህሪያችንን ማስቀጠል ነው። ይህ የመረጃ ሃብት ኤግዚቢሽን ነዋሪዎች መብቶቻቸውን እንዲገነዘቡ ለማስቻል የሚረዱ እና የተዋልዶ ጤናን፤ የስራ ክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችንና የኮንትራት አተገባበር መርሆዎችን ባካተተ መልኩ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ከህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ እና ደህንነት ጋር የተያያዙ የተለያዩ መረጃዎችን ለነዋሪዎች በነጻ ያቀረበ ነበር።    

በኤግዚቢሽኑ መካፈል ያልቻላችሁ በአካባቢ ደረጃ ስለሚገኙ የማህበረሰብ ሃብቶች የሚያትተውን የምክር ቤቱን ድረገጽ / local community resources available for you / በማንበብ መረጃ ልታገኙ ትችላላችሁ።

የምክር ቤቱ ፕሬዚደንት ኬት ስቴዋርት በኤግዚቢሽኑ ላይ ከአንድ የማህበረሰቡ አባል ጋር ሲጨባበጡ የሚያሳይ ፎቶ.

ካውንስሉ ከአናሳ የህብረተሰብ ክፍሎች /minority/ በወጡ ግለሰቦች እንዲሁም በሴቶች እና የአካል ጉዳተኛ ወገኖች ለሚተዳደሩ የንግድ ማእከላት የሚደረግን የቢዝነስ ኮንትራት ልዩ የድጋፍ ፕሮግራም አራዘመ

በካውንቲው ከአናሳ የህብረሰብ ክፍሎች በወጡ ግለሰቦች እንዲሁም በሴቶች እና በአካል ጉዳተኛ ወገኖች ለሚተዳደሩ የንግድ ማእከላት የሚደረግን የቢዝነስ ኮንትራት አሰጣጥ ልዩ የድጋፍ ፕሮግራም / Minority, Female and Disabled-Owned Business Purchasing Program / በአምስት አመት እንዲራዘም የሚጠይቀውን ህግ ከሌሎች የምክር ቤት አባላት ጋር ሆኜ መደገፌን /ኮ ስፖንሰር/ ስገልጽ ኩራት ይሰማኛል። ይህ የማራዘሚያ ህግ በዛ ያሉ ከአናሳ የህብረሰብ ክፍሎች በወጡ ግለሰቦች እንዲሁም በሴቶች እና የአካል ጉዳተኛ ወገኖች የሚተዳደሩ የንግድ ማእከላት የካውንቲውን የግዢ ኮንትራቶችን እንዲወስዱ ለማስቻል ይረዳል። አብዛኛዎቹ እነኚህ የንግድ ተቋማት ለማህበረሰቡ ቁልፍ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ማእከላዊ ስፍራ የያዙ በመሆናቸው ለስራ ፈጠራ እና በአጠቃላይም ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ናቸው። በዚህ አጋጣሚም የንግድ ተቋማትንና በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን በቀጣይነት እንዲሁም ሚዛናዊ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ በእኩልነት ለመደገፍ የሚረዳውን ይህን ፕሮግራም የመሚመሩትን የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚደንት ጂል ጃዋንዶ እና የምክር ቤቱ አባል የሆኑትን ሎውሪ አን ሳይልስ ማድነቅ እፈልጋለሁ።  

በ ዲ ሲ ኔውስ ናው በተሰኘው የዜና ማሰራጫ የቀረበ ርእሰ ዜና “ሞንትጎመሪ ካውንቲ ከአናሳ የህብረሰብ ክፍሎች በወጡ ግለሰቦች ለሚተዳደሩ ንግድ ተቋማት የሚሰጥ የቢዝነስ ኮንትራት በእጅጉ ማደጉን አበሰረ ”.

እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የአገልግሎት ሰጪዎችን  ለመደገፍ የወጣ አዲስ ህገ ረቂቅ

በሲልቨር ስፕሪንግ ማእከላዊ የቢዝነስ ዲስትሪክት አካባቢ ለሚኖሩ ቤት ለሌላቸው ግለሰቦች አገልግሎት ለሚሰጡ የህጻናት እንክብካቤ ሰጪ ሰራተኞችና አገልግሎት አቅራቢዎች የቅናሽ የመኪና ማቆምያ ፈቃድ እንዲሰጥ የሚፈቅደውን ረቂቅ ህግ በቅርቡ ለምክር ቤቱ አቅርቤ ነበር። በሲልቨር ስፕሪንግ ማእከላዊ የቢዝነስ ዲስትሪክት አካባቢ የሚኖሩ፤ የሚሰሩ  እና የሚገበያዩ ሁሉ በአካባቢው በሚካሄደው የመንገድ ግምባታ ስራ ምክንያት በእጅጉ የተጎዱ መሆናቸውና ፕሮግረስ ፕሌስ በተባለው የቤት አልባ ሰዎች መርጃ ማእከል እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ የህጻናት እንክብካቤ ተቋማት ላይም እንዲሁ ተጽእኖ አድርሷል። ይህ በንዲህ እንዳለም በአቅራቢያው የሚገኙ የመኪና ማቆሚያ ጋራጆችም የሚገባቸውን ያህል ጥቅም ላይ መዋል አልቻሉም። የቀረበው የማስተካከያ ቅናሽ በአሁኑ ሰአት በአካባቢው ጋራጆች ከሚሰራበት የወርሃዊ የክፍያ ተመን አምስት በመቶ ቅናሽ ማድረግ የሚል ነው። የሚጸድቅ ከሆነ ይህ እርምጃ በሲልቨር ስፕሪንግ አካባቢ እጅግ አስፈላጊ አገልግሎት ለሚያቀርቡ ተቋማትና ግለሰቦች እፎይታን የሚሰጥ ይሆናል። ረቂቅ ህግ 29-24 በተባለው በዚህ ህግ ላይ የሚደረገው ለህዝብ ክፍት የሆነ ውይይት የሚካሄደው በታህሳስ/ጃኑዋሪ 21 ይሆናል። ዝርዝሩን ይህን በመጫን The public hearing for Bill 29-24 is scheduled for Jan. 21 ያገኛሉ።

በዳውንታውን የሚገኙ ጋራጆች የሚታይ የመኪና ማቆሚያ ምልክት.

ኬት በማህበረሰቡ ውስጥ

የአናሳ ማህበረሰቦች/ማይኖሪቲ የህግ አውጪ አባላት የቁርስ ግብዣ

በ24ተኛው አመታዊ የማይኖሪቲ ህግ አውጪዎች የቁርስ ግብዣ ስነስርዓት /24th Annual Minority Legislative Breakfast / ላይ የተካፈልኩ ሲሆን ይህም ሞንትጎመሪ ካውንቲን በሚመለከቱና በለሎች አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት እና ከስቴት እና ከፌደራል ሃላፊዎች ጋር የሚኖረውን ቅንጅት እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል ሃሳብ ለመለዋወጥ እድል ፈጥሮልኛል።  ይህ በየአመቱ የሚካሄደው ግብዣ ከአፍሪካን አሜሪካን የንግድ ምክር ቤት ፣ ከኤዢያን አሜሪካን የፖለቲካ ጥምረት እና ከሂስፓኒክ የንግድ ምክር ቤት አባላት የሚሰጡ ትምህርትን፤ አቅምን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚነትን፤ የኢኮኖሚ እድገትን፤ የማንነት ፍትሃዊ እኩልነትን፤ ማህበራዊ ፍትህን የተመለከቱ አስተያየቶችንና እና ሌሎችንም ጨምሮ  በአጠቃላይ ከምክርቤት ህግ አውጪ ተግባራት ጋር የተያያዙ ቀዳሚ የጋራ ጉዳዮችን በማንሳት ለመወያየት እድል የሚፈጥር ክስተት ነው።  

የካውንስሉ ፕሬዚደንት ስቴዋርት እና ሴኔተር ቫን ሆለን በማይኖሪቲ የህግ አውጪዎች የቁርስ ግብዣ ላይ ከማህበረሰብ አማራሮች ጋር.

በሲቪክ ሰርክል/ማእከል / The Civic Circle/ የተደረገ ጉብኝት

የሲቪክ ማእከሉ የተስፋ ድምጾች /“Voices of Hope celebration/ የተባለ ስነስርአት ያከበረ ሲሆን በዚህም ዝግጅት ላይ ፕራኒል ሱቫርና ከተባለው የሞንትጎመሪ ካውንቲ የህዝብ ትምህርት ቤቶች /MCPS/ የትምህርት ቦርድ የተማሪዎች ተወካይ አባል ጋር አብሬ በመሳተፌ ክብር ተሰምቶኛል።   በብሄራዊ ደረጃ የሚታየው ፖለቲካዊ መካረር/ polarization/ እና የመረጃ መዛባት መስፋፋት እያደገ በመጣበት በዚህ ወቅት ወጣቶችን በዲሞክራሲ ሂደት እንዲሳተፉ ማበረታታት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስፈላጊነቱ እየጎላ የመጣ ሲሆን ይህም ስራ ደግሞ መጀመር ያለበት ከአካባቢ ደረጃ ጀምሮ ነው።  በመሆኑም ይህ ድርጅት የስነ ዜጋ/ሲቪክ/ ትምህርትን ለመደገፍ እና ቀጣዩ ትውልድም ርህራሄ ያለው፤ በበቂ መረጃ የታነጸ እና ለመብቱ ተቆርቋሪ እና ተሳታፊ የሆነ ዜጋ እንዲሆን ለማስቻል አቅዶ እየሰራ ያለውን ስራ ለማመስገን እወዳለሁ።  

የሲቪክ ሰርክል መስራች ኤሊዛ ኔውሊን ካርኔይ፣ የካውንስሉ ፕሬዚደንት ስቴዋርት እና የተማሪ ተወካይ የትምህርት ቦርድ አባል ሱቫርና በተስፋ ድምጾች ዝግጅት ላይ.

የግሬተር ካፒታል አካባቢ የህንጻ/ቤት ሽያጭ/ኪራይ ኤጀንቶች ማህበር የህግ አውጪ የቁርስ ግብዣ

በሞንትጎመሪ ካውንቲ የሪል እስቴት ኢንዱስትሪ ላይ ተጽእኖ በሚያሳድሩ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በሚደረገው እና  የንግድ ተቋማት ተወካዮች እና የህዝብ ተመራጮች በሚሳተፉበት በአመታዊው የግሬተር ካፒታል የህንጻ/ቤት ሽያጭ/ኪራይ ኤጀንቶች ማህበር /Greater Capital Area Association of Realtors / GCAAR/ / የህግ አውጪ ስብሰባ ላይ የመሳተፍ ጥሩ እድልም አጋጥሞኝ ነበር። ከማህበሩ /GCAAR/ እና ከንግድ ተቋማት ወይንም የኢንዱስትሪ ሃላፊዎች ጋር በመቀናጀት በሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ ተጨማሪ የመኖሪያ ቤት፤ አቅምን ያገናዘቡ የመኖሪያ ቤቶች እና የቤት ባለቤትነት እድሎች እንዲፈጠሩ የሚያግዙ አዳዲስ አሰራሮች/መፍትሄዎችን ለማመንጨት እና ለመተግበር አብረን እንደምንሰራ እጠብቃለሁ።

የካውንስሉ ሬዚደንት ስቴዋርት እና የ/GCAAR ፕሬዚደንት የአሜሪካ እና የሜሪላንድ ባንዲራዎች እና የማህበሩ አርማ በተለጠፈበት ፖስተር  ፊት ለፊት የተነሱት ፎቶ።

የአእምሮ ጤናን በተመለከተ

በበአል ወቅት የሚፈጠር የስሜት መጫጫንን ማስወገድ

አመት በአላት ከቤተሰብ አባላት እና ከሌሎች የቅርብ ወዳጆች ጋር በመሆን የማሕበራዊ ትስስር የመፍጠሪያ እንዲሁም  የደስታ እና የፈንጠዝያ ወቅቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ደግሞ ለአብዛኞቻችን በአላት ተጨማሪ ጭንቀት እና የተመሰቃቀሉ ስሜቶችን ይዘውብን ሊመጡ ይችላሉ። በበአላት ወቅት እንዲህ አይነት አስደሳች ያልሆነ ነገር ከገጠመዎት ለዚህ አይነቱ ክስተትም የሚረዱ እገዛዎች እንዳሉ ሊያውቁ ይገባል።  ይህን / Strategies for managing holiday stress / የሚለውን ድረግጽ ሲጫኑ ለራስዎ ጊዜ መስጠትን፤ ከውድ/የቅርብ/ ታማኝ/ ወዳጆች  ጋር መገናኘት፤ እና ጤናማ የሆነ የበአል አከባበር ሂደትን መከተል የሚሉትን ጨምሮ በርካታ ከበአል ቀናት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ጭንቀቶችን ለመቋቋም የሚረዱ ዜዴዎችን ያገኛሉ። እራስዎም ወይንም ሌላ እንዲህ አይነቱ ችግር ያጋጠመውን ሰው የሚያውቁ ከሆነ ወደ በ9-8-8 የብሄራዊ አጣዳፊ ችግር ልዩ መስመር / National Crisis Hotline/ በመደወል ወይንም የስልክ መልእክት በመላክ መረጃ ማግኘት የሚችሉ ሲሆን ለሞንትጎመሪ ካውንቲ ደግሞ በ (301) 738-2255 የአጣዳፊ ችግር የልዩ መስመር መደወል ወይንም የስልክ መልእክት መላክ ይችላሉ። ተጨማሪ የአእምሮ ጤናን የተመለከቱ መረጃዎችን ለማግኘት mental health resources are available through the County web page የሚለውን ድረገጽ ይጫኑ።

የ988 የራስ ማጥፋትንን እና አጣዳፊ ጉዳትን የማሳወቂያ መስመር