ውድ ጓደኞቼ፣
የካውንስሉ የበጀት የስራ ሂደት በሙሉ ሃይል እየተካሄደ ሲሆን በአሁኑ ሰአትም በካውንቲው ስራ አስፈጻሚ ለ2026 የቀረበውን የ7.7 ቢሊዮን ዶላር የስራ ማስኬጃ በጀት በመመርመር ወይንም በመከለስ ላይ እንገኛለን። ታይቶ በማይታወቅ እና በተዛባ ሁኔታ በፌደራል መንግስቱ እየተካሄደ ባለው የበጀት ቅነሳ እና ያንንም ተከትሎ በእስቴቱ እየተደረገ ባለው በጀትን የማሸጋሸግ ሂደት ምክንያት እያንዳንዱ ዶላር ለካውንቲያችን እጅግ በጣም በሚጠቅም ሁኔታ መዋሉን ማረጋገጥ ይኖርብናል። በመሆኑም በአሁኑ ሰአት የኛ አላማ ለነዋሪዎቻችን ዋስትና የሆኑትን የሴፍቲ ኔት አገልግሎቶች፣ የህዝብ ደህንነት እንዲሁም የዛሬ እና የወደፊቱንም የትምህርት አቅርቦት ሁኔታ ለማገዝ የምናደርገውን ያላሰለሰ ጥረት እና ቁርጠኝነት አጠናክሮ ማስቀጠል ይሆናል።
እንደሚታወቀው ነዋሪዎቻችን እያደገ ለመጣው የንብረት ታክስ እየተጋለጡ በመሆኑ ካውንስሉ የሞንትጎመሪ ካውንቲ የንብረት ታክስን በተመለከተ የማያገዳድር አቋም በመያዝ በተለይ የንብረት ታክስን ላለመጨመር ቁልፍ የሆነ የመጀመሪያ ውሳኔ ላይ ደርሷል።
ሚያዚያ 22 የካውንቲው ስራ አስፈጻሚ ከኋላ ጀምሮ የሚታሰብ የገቢ ግብር ጭማሪ እንዲደረግ የሚል የውሳኔ ሃሳብ ለካውንስሉ ልከው ነበር። በመሆኑም ለማህበረሰቡ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን በቀጣይነት ለማቅረብ የሚያግዝ ገንዘብ ለመሰብሰብ አንድ አማራጭ ይሆናል በሚል የገቢ ግብር መጠኑ አሁን ካለው 3.2 ፐርሰንት ወደ 3.3 ፐርሰንት እንዲቀየር በሚል የካውንቲው ስራ አስፈጻሚ ባቀረቡት ሃሳብ ላይ ካውንስሉ ግምቦት 13 ህዝባዊ ውይይት ያካሂዳል።
ካውንስሉ የነዋሪዎቻችንን መሰረታዊ ፍላጎት ማእከል አድርጎ መስራት የሚለውን ባህል ለማስቀጠል የሚሰራ ሲሆን በተጓዳኝም በመላ ሃገራችን የሚሰራበትን በጥሩ ሁኔታ የማስተዳደር መስፈርትን የሚለካውን የኤኤኤ ቦንድ ደረጃችንን በሚያስጠብቅ መልኩ ሃላፊነት የተሞላው የበጀት አስተዳደር ስራችንንም ለማስጠበቅ እንጥራለን። እስካሁን ጠብቀን ያቆየነውን እና ከገንዘብ አስተዳደር አኳያ ውጤታማ የተባሉትን የኢኮኖሚ መርሆዎች ጠብቀን መጓዝም ከፊታችን የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች በተገቢው መልኩ ለመወጣት የሚረዳን ይሆናል።
ከሰላምታ ጋር፣
ኬት ስቴዋርት
የካውንስሉ ፕሬዚደንት
የካውንስል አባል ከሆኑት ክሪስቲን ሚንክ እንዲሁም ጊልበርት ኢምፕሎይመንት ሎው እና ፌደራል ዩኒየኒስት ጥምረት ከተባሉ ት ድርጅቶች ከተውጣጡ ባለሞያዎች ጋር በመሆን ዛሬ ግምቦት 7 ምሽት በ 7 ፒ ኤም ላይ በ ዙም ድረ መረብ በሚካሄድ የለአገልግሎት እና እገዛ እንተባባር በተባለው የማህበረሰብ ስብሰባ ላይ እካፈላለሁ። ውይይቱ የሚያተኩረው “እንዴት እንታገል፤ በፌደራል ደረጃ የመብት ጥብቅና መቆም እና መብቶችን ለመገንዘብ ላይ ውጤታማ በሆነ መልኩ መሳተፍ” በሚል ርእስ ላይ ነው።
ይህ የኦንላይን መድረክ ባለፉት ጊዜያት በተከታታይ በየሁለት ሳምንቱ በካውንቲው በተደረጉ እና በስራ ቅጥር፣ በሰው ሃይል ልማት እና የስራ አጥነት ጥቅማጥቅሞች፣ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች፣ የመኖሪያ ቤት እገዛ፣ የጤና እና ደህንነት እንዲሁም መሰረታዊ በሆኑ የካውንቲ አገልግሎቶች ላይ ካተኮሩት ተከታታይ የውይይት መድረኮች መካከል ስድስተኛው ውይይት ነው።
የሞንትጎመሪ ብሌር የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጁኒየር የሆነችውን አኑቫ ማሎ ለ2025-2026 የትምህርት ዘመን በትምህርት ቦርዱ ውስጥ የተማሪ ተወካይ የቦርድ አባል ሆና በመመረጧ እንኳን ደስ አለሽ ብለናታል! በአባልነትሽ በመጪው አመት የሞንትጎመሪ ካውንቲ የህዝብ ትምህርት ቤቶች / MCPS/ ተማሪዎችን ወክለሽ የምታከናውኚያቸውን ነገሮች ሁሉ ለማየት እንሻለን።
በተጨማሪም በመጪው ሰኔ ከክላርክስበርግ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚመረቀውንና የቦርድ አባልነቱን ያጠናቀቀውን ተማሪ ፕራኔል ሱቫርናን ለማመስገን እንወዳለን።
በ50ኛው አመታዊ የህዝብ ደህንነት ሽልማቶች አሰጣጥ ስነስርአት ላይ ከሜሪላንድ ስቴት ገዢ ዌስ ሙር፣ የኮንግረስ አባል ጄሚ ራስኪን፣ ኮምፕትሮለር ብሩክ ሊርማን፣ የካውንቲው ስራ አስፈጻሚ ማርክ ኢርሊች፣ እንዲሁም ከሌሎች የምክርቤት የስራ ባልደረቦቼ እና የህዝብ ደህንነት ባለስልጣናት ጋር አብሬ በመገኘቴ ክብር ተሰምቶኛል። እነዚህ ሽልማቶች በስራው ላይ እንዳለ ለህይወቱ ሳይሳሳ ስራውን በመስራት ላይ እያለ በፍጥነት ያሽከረክር በነበረ ሾፌር በመኪና የተገጨው እና ለዚህም ጀኝነት ለተላበሰው ስራው የወርቅ የሽልማት ያገኘው ሳጅን ፓትሪክ ኬፕን እና እሱን ለመሳሰሉ እና ለህይወታቸው ሳይሳሱ ከሚፈለገው በላይ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሴት እና ወንድ ጀግኖች የሚሰጡ በረከቶች ናቸው። ሁላችሁንም መኮንኖች እና የመጀመሪያ ደረጃ የአደጋ ደራሽ ሰራተኞች ለነዋሪዎቻችን እና ለአጠቃላይ የህዝባችን ደህንነት ለምትሰጡት አገልግሎት፣ መስዋእትነት እንዲሁም ለማያወላውል ቁርጠኝነታችሁ ላመሰሰግናችሁ እወዳለሁ።
በትላንትናው እለት ካውንስሉ ግንቦት የጄዊሽ አሜሪካውያን የመታሰቢያ ወር እንዲሆን እውቅና ሰጥቷል። ሞንትጎመሪ ካንቲ በስቴቱ ውስጥ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ጄዊሽ አሜሪካውያን የሚኖሩበት ካውንቲ እንደመሆኑ መጠን የጂዊሽ አሜሪካውያንን ቅርስ እና ታሪክ እንዲሁም የአይሁድ አሜሪካውያን ለካውንቲው፣ ለስቴቱ እና በአጠቃላይም ለሃገሪቱ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ሞንትጎመሪ ካውንቲ በኩራት በማሰብ ያከብራል።
በሞንትጎመሪ ካውንቲ ውስጥ በአካታችነት፣ በመተሳሰብ እንደምናምን እና ይህን የተሰባጠረ ማህበረሰባችንን የሚያንጸባርውን የዳበረ ባህላችንን እንደምናስቀጥል ለመግለጽ እንወዳለን።
በ2019 በተከሰተ በጣም አውዳሚ ለሆነ ጎርፍ ተጋልጦ የነበረው እና በአዲስ መልኩ የታደሰው እና በጥንክሬው የሚታወቀው የስኮትላንድ ኤ ኤም ኢ ጽዮን ቤ/ክርስቲያን ለአማኞች እና ለማህበረሰቡ ክፍት ሆኗል። የዚህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን መታደስ እና ወደነበረበት መመለስ የስኮትላንድ ማህበረሰብን ጥንካሬ የሚያሳይ ሲሆን በጥምረት የሚሰራ ስራ ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋን ለማስረጽ ምን ያህል ሃይል እና አስተዋጾ እንዳለው የሚያሳይ ነው።
የሞንትጎመሪ ካውንቲ የመሬት ቀንን በመላው ካውንቲ ውስጥ የተለያዩ ክስተቶችን በማዘጋጀት አክብሯል። በዊተን በተካሄደው አመታዊው ‘ግሪን ፌስት’ ፈስቲቫል ላይ በመገኘት እና በሎንግ ብራንች የመሬት ቀን አከባበር ላይም አበባ በመትከል በመሳተፍ አርኪ ጊዜ አሳልፌያለሁ። የካውንስሉ የትራንስፖስት እና የአካባቢ ጥበቃ ኮሚቴም የመሬት ቀንን በክብር ለማሰብ በሚል የወደፊት ፖሊሲዎቻችን እና ስራዎቻችን ዘላቂነትን መሰረት ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባቸው እና ከካርቦን ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር በድጋሚ ቃል መግባት አለብን የሚለውን ድንጋጌ በአዋጅ መልክ አቅርቧል።
እጅግ በጣም የተዋጣላቸው እና ለሞንትጎመሪ ካውንቲ ታላቅ ኩራት እና ክብር ያጎናጸፉ አትሌቶች የሚከበሩበትን የሞንትጎመሪ ካውንቲ የዝነኛ ስፖርተኞች የማክበር ስነስርአት ላይ በመገኘቴ ተደስቻለሁ። ዝነኛ ስፖርተኞችን የማክበር ስነስርአቱ በህይወት ለሌሉት እና የልዩ ኦሊምፒክ መስራች ለሆኑት እንዲሁም እድሜያቸውን ሙሉ የአእምሮ እክል ላለባቸው ሰዎች ጥብቅና በመቆም የታገሉትን ዩኒስ ኬኔዲ ሽራይበር የመጀመሪያ የህይወት ዘመን ስኬት ሽልማት የድህረ ሞት ተሸላሚ አድርጓል። በ2025 ለተሸለሙ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ!
የኪንግስበሪ የደህንነት እና የመማማር ቡድን የመማር እክሎች እና የባህሪ ችግር ያሉባቸው ቤተሰቦች ላይ ትኩረት በማድረግ እነኚህ ወገኖች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች/ ፈተናዎች ለመቅረፍ እና እምቅ ሃይላቸውንም ማውጣት እና መጠቀም እንዲችሉ ለማገዝ የሚሰራ ለትርፍ ያልተመሰረተ ድርጅት ነው። ኪንግስበሪ በሞንትጎመሪ ካውንቲ ለሚኖሩ ቤተሰቦች እና ሌሎችም በአካባቢው የሚኖሩ እና የመግዛት አቅም ላላቸው ግለሰቦች በጣም ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የስነልቦና አገልግሎቶችን በገበያ ዋጋ የሚያቀርብ ሲሆን የሚገኘውንም የአገልግሎት ክፍያ በመጠቀም ሌሎች የመክፈል አቅም ለሌላቸው ቤተሰቦች አገልግሎቱን ለማቅረብ ይጠቀምበታል። ቡድኑ የእያንዳንዱን ግለሰብ ፍላጎት በተለየ ሁኔታ በሚያሟላ መልኩ ለማገዝ ሆን ተብለው የተቀረጹ የአሰራር ዘዴዎችን በመጠቀም ለህጻናት፣ ለጎረምሳ እድሜ ላይ ላሉ እንዲሁም ለአዋቂዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ ይገኛል። በመጪው ነሃሴም የህይወትን ተግዳሮቶች አላማን እና ግልጽነትን ባተኮረ መልኩ እንዲወጡ ለማድረግ የሚረዳ እና “ሰዎች በስራ ላይ” የተባለ ልዩ የሆነ የ15 ሳምንት ፕሮግራም ይጀምራሉ።
ግምቦት የአእምሮ ጤና ግንዛቤ ወር መሆኑን ያውቁ ኖሯል? በማንኛውም የእድሜ ክልል ላይ እያሉ የአእምሮአዊ ጤንነትዎን መንከባከብ በጣም ጠቃሚ መሆኑን እና ነገር ግን ደግሞ እድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ የአእምሮ ጤናን መከባከብ ለአጠቃላይ ጤንነታችንን እና ህይወታችን ወሳኝ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። በቅርቡ የአሜሪካ ሙስሊሞች የእድሜ ባለጸጋዎች ማህበር /ኤ ኤም ኤስ ኤስ/ (AMSS) እና በቦልቲሞር የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ የአረጋውያን እና የእርጅና ሳይንስ ትምህርት እና ጥናት ምረቃ ፕሮግራም ስር የሚገኘውን እና ትምህርት፣ በጥናት እና ስልጠናን በመጠቀም ለአረጋውያን የሚሰጠውን የንክብካቤ የአገግሎት ጥራት ለማሻሻል የሚረዳውን ባህል ተኮር የአእምሮ ጤና ስርአተ ትምህርት ማሳደጊያ ፕሮግራምን በቅርቡ ጎብኝቻለሁ። ኤ ኤም ኡእስ ኤስ በበቂ ሁኔታ አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ እድሜያቸው የገፋ አዋቂዎች እና እንክብካቤ ሰጪዎች መልካም ህይወት ለመምራት የሚያስችሏቸውን ግብአቶች በማቅረብ ብቁ እንዲሆኑ ይጥራል።