ውድ ጓደኞቼ፤
የሞንትጎመሪ ካውንቲ ምክር ቤት $7.6 ቢሊዮን ዶላር የሆነውን የካውንቲውን የ2026 የበጀት አመት የስራ ማስኬጃ እና $6 ቢሊዮን የሆነውን የ2025-30 ዓ ም የተሻሻለ የካፒታል ማሳደጊያ ፕሮግራም በጀት ድምጽ በመስጠት አጽድቋል።
በዚህ አመት በጀት ላይ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ፈተናዎች አጋጥመውናል። እነኚህን ፈተናዎች ለማሸነፍም አካታች፣ ግልጽ እና ትብብር የተሞላበት የአሰራር ሂደትን የተከተልን ሲሆን በዚህም ምክንያት በመጨረሻ ምንም የግብር ጭማሪ ማድረግ ሳያስፈልግ ለነዋሪዎቻችን አግባብ ያለውን ውጤት ማምጣት ችለናል።
በቀላሉ ለማስቀመጥ ያህል በማህበረሰባችን ውስጥ የሚከሰቱት የነዋሪዎቻችን ፍላጎቶች እየጨመሩ ሲሆን ለመውሰድ የተገደድናቸውም ውሳኔዎችም በዛው መሰረት ከበድ ያሉ ነበሩ። የትራምፕ ፕሬዚደንታዊ አስተዳደር ከጀመረ ገና አምስት ወር እንኳን ሳይሞላው ሞንትጎመሪ ካውንቲ፣ ሜሪላንድ ስቴት በራሱ እንዲሁም መላ አካባቢው ለአስርት አመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የመጠራጠር ሁኔታ እየገጠማቸው ነው። ቤፌደራል ደረጃ የተደረጉ የበጀት ቅነሳዎች የሁላችንም ኑሮ/ህይወት እንዲሁም መላው ነዋሪዎቻችን የሚመኩባቸው ማናቸውንም ህዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ተጽእኖ እያደረጉ ሲሆን ወደፊትም ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።
ይህም ቢሆን ግን እኛ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይ እና አካታች የሆኑትን እሴቶቻቸንን በጽናት በማስቀጠል እንዲሁም እየለመለመ ያለ እኮኖሚያችንን እና እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የትምህርት ስርአታችንን በማስቀጠል ወጣት ነዋሪዎቻችን እና በአጠቃላይም ቤተሰቦቻችን ጥሩ የወደፊት ህይወት እንዲኖራቸው ለማዘጋጀት ብርቱ ጥረት እናደርጋለን።
የ2026 ዓ ም በጀታችንም ይህንኑ የሚያመለክት ነው። በተያያዘም ከዚህ በታች ያሉትን የተወሰኑ ማሳያዎችን ስዘረዝር ኩራት ይሰማኛል፤
ትምህርትን በተመለከተ፤
- የሞንትጎመሪ ካውንቲ የህዝብ ትምህርት ቤቶች / MCPS / በጀት እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ $3.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፤ ይህም ከአጠቃላዩ የካውንቲው ባጀት ግማሹን የሚሆን ሲሆን በሞንትጎመሪ ካውንቲ ት/ቤቶች ከቀረበው የባጀት ጥያቄ ውስጥ 99.8% የሚሆን ነው።
- ለሞንትጎመሪ ኮሌጅ $345 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ ሲሆን ይህም አሁን ያላቸውን የማስተማር ደረጃ ጠብቀው ለማቆየት የሚያስችላቸው ነው።
የህዝብ ሰላም/ደህንነትን ማስጠበቅ
- ለሞንትጎመሪ ካውንቲ የፖሊስ መምሪያ የተደረገ የ$352 ሚሊዮን ዶላር በጀት፤ በተጨማሪም በጣም ውጤታማ የሆነውን በድሮን የታገዘ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሰጪ/ደራሽ ፕሮግራምን ወደ ጀርመንታውን ለማስፋፋት የተደረገውን ድጎማንም ያካትታል።
- ለአደጋ ጌዜ አስተዳደር እና የአገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ /Office of Emergency Management and Homeland Security/ የተደረገ የበጀት ጭማሪ። ይህም ድጎማ ከፌዴራል መንግስት የሚመጡ ድጎማዎች ቅነሳ እና ሙሉ በሙሉ መቋረጥ ባጋጠመበት በአሁኑ ወቅት የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ እቅድ አወጣጥን፣ ስልጠናን፣ የአገልግሎት ማዳረስ ስራዎችን ለማስቀጠል ይረዳል በሚል ታስቦ ነው።
- ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችን እንዲሁም የእምነት ድርጅቶችን እና የማምለኪያ ተቋማትን ከጉዳት ለመጠበቅ ለተቋቋመው “ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች የሴኩሪቲ ድጎማ ፕሮግራም” የተደረገ የ$1.2 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ።
የጤና አና የስብአዊ አገልግሎቶች መስሪያ ቤት
- እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ የምግብ አቅርቦቶችን ለማድረግ እንዲረዳ ለምግብ አቅርቦት ስርአት ማረጋጊያ ቢሮ / Office of Food Systems Resilience / የ $14 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ
- በሞንትጎመሪ ካውንቲ እያደገ የመጣውን የቤት አልባነት ችግር ለመፍታት በታቀዱ የ “ቤት አልባነትን የማጥፋት እና የመከላከል” አገልግሎቶች የተደረገ የ$62 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ
- ሕጻናትን፣ ወጣቶችን እና ቤተሰቦችን ለመደገፍ ለታቀዱ አገልግሎቶች የሚሆን የ$140 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ እንዲሁም አረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞችን ለመርዳት የታቀዱ አገልግሎቶችን ለማገዝ የተደረገ የ$78 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ
- ለስነባህሪ ጤና እና የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶች፣ ለአእምሮ ጤና ማስፋፊያ አገልግሎቶች፣ ለህክምና እና ማገገም አገልግሎቶች አንዲሁም የስነባህሪ ጤና ችግር ላለባቸው በሁሉም እድሜ ክልል ለሚገኙ ሰዎች ለሚሰጡ አገልግሎቶች የተደረገ የ$66 ሚሊዮን ድጎማ
- በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኬፌደራል መንግስቱ ተደጋጋሚ እና እየጨመረ በመጣው በጀት ቅነሳ ባለበት ሁኔታ የህብረሰብ ጤና መምሪያችን በጣም ጠቃሚ የሆኑ የተዋልዶ ጤና አና የኤች አይ ቪ/በግብረስጋ የሚተላለፉ በሽታዎችን ምርመራ አገልግሎቶች ጨምሮ በአጠቃላይ በሴክሿል ጤና አገልግሎቶች አሰጣጥ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት የሚያደርገውን ትኩረት እና እገዛ በማስብበት ጊዜ ኩራት ይሰማኛል።
የኢኮኖሚ እድገት
- ካውንስሉ በስራ ፈጠራ፣ በገበያ ፍለጋ/መሳብ እና ቢዝነስ ልማት ላይ ላተኮሩ የልማት ፕሮግራሞችን ያጸደቀ ሲሆን ለካውንቲው ግምባር ቀደም የኢኮኖሚያዊ ልማት ድርጅት ለሆነው የሞንትጎመሪ ካውንቲ የኢኮኖሚያዊ ልማት ኮርፖሬሽን (MCEDC) የ$5.3 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ አድርጓል።
- ወርክፎርስ ሞንትጎመሪ ለተባለው እና በአሁኑ ሰአት ስራ በመፈለግ ላይ ያሉ የፌዴራል ሰራተኞችን ለማገዝ ለሚሰራው ድርጅት የ$3.2 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ
የመጓጓዣ አገልግሎቶች፣ ፓርኮች እና አካባቢ ጥበቃ
- በዚህ አመት ከመጓጓዣ አገልግሎት ፍትሃዊ አቅርቦት እና ከአካባቢ ጥበቃ ትልሞቻችን ጋር በተገናዘበ መልኩ እንዲሁም የተሳፋሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ እና ለማበረታታት በማሰብ የራይድ ኦን አገልግሎቶችን ለሁሉም ነዋሪዎች ነጻ አድርገናል።
- እጅግ በጣም ዋጋ የሚሰጣቸው እና የማህበረሰባችን መገለጫ ሃብት በሆኑት በፓርኮቻችን በጀት ላይም ሊደረጉ የታሰቡ ቅነሳዎችንም ውድቅ አድርገናል፤ እንዲሁም ለአዲሱ የሲልቨር ስፕሪንግ የመዝናና እና የውሃ መዝናኛ ማእከል/አኳቲክ ሴንተርን ጨምሮ ለሞንትጎመሪ መዝናኛም የሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ እንዲጨመር አድርገናል።
- በአየር ንብረት ለውጥ/አካባቢ ጥበቃ ላይ የምንሰራውን ስራ ቀጣይነት ለማረጋገጥም ለግሪን ባንክ በድምሩ $17 ሚሊዮን ዶላር እንዲመለስ እና እንዲሰራበት መድበናል።
የመኖሪያ ቤትን በተመለከተ
- አቅምን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሳደግ እና ጠብቆ ለማቆየት በማሰብ ለመኖሪያ ቤት እና የማህበረሰብ ጉዳዮች መስሪያ ቤት (DHCA) የ$81.4 ሚሊዮን ዶላር መድበናል።
- ለመኖሪያ ቤት ኢኒሺየቲቭ ፈንድ ፕሮግራም የ $58 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ የተደረገ ሲሆን ይህም የኪራይ ክፍያ እገዛን ለማሳደግ እንዲሁም በካውንቲው ውስጥ አቅምን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤቶችን ፋይናንስ ለማድረግ ፣ ለመገንባት እንዲሁም ጠብቆ ለማቆየት ያግዛል።
- ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ ቤተሰቦችን ህይወት ለማሻሻል እና ለማሳደግ የሚረዱ አገልግሎቶችን ለሚሰጠው ‘ለመኖሪያ ቤትኢድል ፈጠራ/አቅርቦት/ ድርጅት’ / Housing Opportunities Commission/ የ$9 ሚሊዮን ዶላር ድጎማ ተደርጓል።
ይህን ሁሉ ለማሳካት የቻልነው በተጓዳኝ ጠንካራ ሰራተኛ ለሆኑት የሞንትጎመሪ ካውንቲ ተቀጣሪዎቻችን ማደግ የምናደርገውን የተለያየ ጥረት እና እገዛ ለማጠናከር ያለንን ቁርጠኝነት በማሳደግ እንዲሁ በምንም መልኩ የግብር መጠን እንዲጨምር ሳናደርግ ነው።
በህዝባዊ የበጀት ውይይቱ ላይ በቀጥታ ምስክርነት ለሰጣችሁ ከ300 በላይ ለምትሆኑ ነዋሪዎች እንዲሁም በእሜይል እና በስልክ ለተሳተፋችሁ እና በባጀት ወቅቱ ሁሉ በአካል ላገኛችሁን በሙሉ በድጋሚ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ከማክበር ሰላምታ ጋር
ኬት ስቴዋርት
የካውንስሉ ፕሬዚደንት
ኬት በማህበረሰቡ ውስጥ
የኤዥያን አሜሪካን፣ የኔቲቭ ሃዋይያን እና የፓሲፊክ አይላንደር (AANHPI) የመታሰቢያ ወር
ሞንትጎመሪ ካውንቲ የግንቦት ወርን እንደ የኤዥያን አሜሪካን፣ የኔቲቭ ሃዋይያን እና የፓሲፊክ አይላንደር (AANHPI) እደመታሰቢያ ወር በመቁጠር ሲያከብር ኩራት ይሰማዋል። ካውንስሉ የኤዥያን አሜሪካን፣ የኔቲቭ ሃዋይያን እና የፓሲፊክ አይላንደር (AANHPI) የመታሰቢያ ወርን የሚያከብረው “የአመራር አና የጽናት ተምሳሌት” በሚለው የዚህ አመት መሪ ጭብጥ/መሪ ቃል ስር ነው። መሪ ቃሉ የወደፊት ትውልዶች በለውጥ እና በስብጥር ጋር እየተለማምመዱ እንዲያድጉ እና እንዲያብቡ የሚያስችል መሰረት የጣሉትን የኤዥያን አሜሪካን፣ የኔቲቭ ሃዋይያን እና የፓሲፊክ አይላንደር (AANHPI) መሪዎች ጠንካራ ስራ እና ጥረት በክብር ለማሰብ የተቀረጸ ነው።
የኤኤኤኤችፒ የመታሰቢያ ወርን ለማሰብ የተዘጋጀውን ቪዲዮ እዚህ ይመልከቱ