ውድ ጓደኞቼ
የመስከረም ወር የአፍሪካን ቅርስ መታሰቢያ ወርን እንዲሁም የእስፓኒሽ ቅርስ መታሰቢያ ወርን በምክርቤታችን የምናከብርበት በመሆኑ መሥከረም የክብረበአላት ወር ነው ማለት እንችላለን።
ያውቁ ኖሯል? ሞንትጎመሪ ካውንቲ የመስከረም ወር በኦፊሴላዊ ደረጃ የአፍሪካን የቅርስ መታሰቢያ ወር እንዲሆን በመሰየም በሃገሪቱ ውስጥ የመጀመሪያው በመሆን ታሪክ መስራት ችሏል። ባለፈው ሳምንት ለአምስተኛ ጊዜ ይህን አመታዊ በአል በልዩ ሁኔታ ያከበርን ሲሆን ለማህበረሰባችን በተለየ መንገድ አስተዋጾ እያደረጉ ያሉ የተለያዩ የማህበረሰብ እና የንግድ ተቋማት መሪዎችን የሚዘክር ቪዲዮም አዘጋጅተናል።
ከዚህ በተጨማሪም የሞንትጎመሪ ካውንቲ የስፓኒሽ ቅርስ መታሰቢያ ወርን ማክበሩን በኩራት እየገለጸ ይህም የሚከበረው ከመስከረም 15 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 15 ባሉት ቀናት ውስጥ ነው። እኔም ከላቲን አሜሪካን አማካሪ ቡድን / Latin American Advisory Group/ ጋር በመሆን የሂስፓኒክ ቅርስ መታሰቢያ ወርን የማክበር ክብር አግኝቻለሁ። በመሆኑም ለማህበረሰብ መሪዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ የመብት ተከራካሪዎች እንዲሁም ነዋሪዎች በአጠቃላይ ለምታደርጉት አስተዋጽኦ እና በዚህም እንቅስቃሴያችሁ ካውንቲያችን ንቁ የሆነ ማህበረሰብ ስብጥር እንዲሆን ስላስቻላችሁት ላመሰግን እወዳለሁ። በሞንትጎመሪ ካውንቲ የሂስፓኒክ ማህበረሰብ አባላትን ለማክበር ወሩን ሙሉ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ እጠብቃለሁ።
በመጨረሻም የሮሽ ሃሻናህን በአል ለሚያከብሩ ሁሉ መልካም አዲስ አመት እመኛለሁ። አመቱ የጤና፣ የደስታ እና የሰላም እንዲሆን የሞቀ ምኞቴንም አንዲሁ መግለጽ እወዳለሁ። ሻናህ ቶቫህ!
ከሰላምታ ጋር
ኬት ስቴዋርት
የካውንስል ፕሬዚደንት
አርብ መስከረም 26 ቀን በዳውንታውን ሲልቨር ስፕሪንግ ለሚካሄደው ሶስተኛው አመታዊ የ”ባኬትስ ኤንድ ቢትስ” የሲልቨር ስፕሪንግ የወጣቶች የመንገድ ላይ ፓርቲ / “Buckets and Beats: Silver Spring Youth Block Party/ ዝግጅት ከኛ ጋር አብራችሁ እንድትገኙ እንጋብዛለን። በነጻ የሚገባበት ይሀው ፓርቲ ተማሪዎች ቀደም ብለው ከትምህርት እንደተለቀቁ ከ 2 ፒ ኤም እስከ 6 ፒ ኤም በቬተራንስ ፕላዛ ይካሄዳል። በዚህ ዝግጅት ላይ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እድሜ ላይ ያሉ ተማሪዎች በፒክልቦል እና ቅርጫት ኳስ ውድድሮች (እዚህ ይመዝገቡ) እና የስነጥበብ/አርት ስራዎች ላይ የሚሳተፉ ሲሆን በመድረክ ላይ በቀጥታ የሚዘጋጅ የዲጄ ሙዚቃ፣ ምግብ እና የተለያዩ ሽልማቶችም ይሰጣሉ።
የሲልቨር ስፕሪንግ የሪጅናል አገልግሎት መስጫ ቢሮን ጨምሮ ሁሉም አጋሮቻችን በየአመቱ አብረው በመሰባበብ ይህን አከባበር እውን ስላደረጉልን ለማመስገን እወዳለሁ። ሁላችሁም ወደዚህ ዝግጅት እንድትመጡ እና ጥሩ ጊዜ እንድታሳልፉ እንጋብዛለን!
ባለፈው ሳምንት ካውንስሉ የህጻናት እንክብካቤ ሰጭ የንግድ ተቋማት በስራ ላይ እንዲቆዩ የሚያስችላቸውን የንብረት ታክስ ክሬዲት አገልግሎት ለማስፋፋት የታለመውን ረቂቅ ህግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል። ይህንን አሁን የሚሰራበትን የህጻናት እንክብካቤ የታክስ ክሬዲት ብቁነት የሚያስፋፋ እና ለነዚህ አካላትም የሚፈቀደውን የክሬዲት መጠን ከ$3,000 እስከ $10,000 የሚያሳድገውን ህግ ስፖንሰር ሳደርግ ኩራት ተሰምቶኛል። ይህ የህጻናት እንክብካቤ አገልግሎት ሰጪዎቻችንን የመደገፍ ተግባር ነዋሪዎቻችን በካውንቲው ውስጥ በተረጋጋ ሁኔታ መስራት እና መኖር እንዲችሉ ያግዛል።
ካውንስሉ በቅርቡ ሁለት የህዝብ ችሎቶችን በማካሄድ የዩኒቨርሲቲ ቡሊቫርድ ኮሪደር ፕላንን በተመለከተ ከ80 ግለሰቦች ምስክርነትን ሰምቷል። የቀረበው ፕላን በዩኒቨርሲቲ ቡልቫርድ የሶስት ማይል መንገድ ላይ የትራፊክ ደህንነትን፣ የአካባቢ ዘላቂነትን፣ እድገት እና የኢኮኖሚ ልማትን የተመለከቱ ጉዳዮችን ለማሻሻል እንደሚረዳ ይታመናል። የካውንስሉ የእቅድ አውጪ፣ የቤቶች እና ፓርኮች ኮሚቴም / Planning, Housing and Parks (PHP) Committee / እቅዱን በተመለከተ መከለስ እና መወያየት በመስከረም 29 ይጀምራል። ኮሚቴው ክለሳውን እንደጨረሰ ካውንስሉ የተግባር ስብሰባዎችን በማካሄድ እና የፕላኒንግ ቦርዱን ረቂቅ ፕላን እንደገና በመፈተሽ ማሻሻያዎችን የሚያደርግ ሲሆን ከዚህም በመቀጠል ማሻሻያዎቹን በተመለከተ ድምጽ የመስጠቱ ሂደት በመጪው መሀር ወቅት መጨረሻ አካባቢ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።.
በመሆኑም ጊዜያቸውን ሰውተው በህዝብ ችሎቱ ላይ በመሳተፍ በእቅዱ ላይ ያላቸውን አስተያየት በመስጠት ለተባበሩን ተናጋሪዎች እና ነዋሪዎች ምስጋና ማቀረብ እወዳለሁ። በተጨማሪም በመስከረም 10 የተካሄደውን የህዝብ ችሎት በማዘጋጀት ለተባበሩን የሞንትጎመሪ ብሌር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ባልደረቦች ቡድን ካውንስሉ አድናቆቱን ለመግለጽ ይወዳል።
ባለፈው ሳምንት “ከሞንትጎመሪ ሂስትሪ” ጋር በመቀናጀት ልዩ የፓነል ስብሰባ ያዘጋጀሁ ሲሆን በስብሰባውም የሞንትጎመሪ ካውንቲን 250ኛ አመት በማንሳት ስለ ታሪኩ እና ባህሉ ሃሳቦችን ተለዋውጠናል።
በ2026 ሞንትጎመሪ ካውንቲም እና ዩኤስ አሜሪካ ሁለቱም 250ኛ አመታቸውን ያከብራሉ። ይህን በአካባባቢም በሃገር አቀፍ ታሪክም አብይ የሆነውን አከባበር ለማስጀመር አንድ ፓነል ውይይት የመራሁ ሲሆን በውይይቱም ታሪክን የማወቅ እና የመመራመርን ጥቅም፣ እንዴት ይህ ታሪክ የአሁኑን ካውንቲ እንደሚገራው እንዲሁም እንዴት ያለፈው ክስተት የአሁኑን እና የወደፊት እርምጃዎቻችንን እና ማህበረሰቦቻችንም ላይ ተጽእኖ እንደሚያደርግ አንስተን ተወያይተናል።
በዚህም አጋጣሚ የሴቶች ኮሚሽነር እና ሊቀመንበር ሺና ፎስተር፣ ተጠባባቂ የታሪክ ጥበቃ ክፍል ሃላፊ ለሆኑት ረበካህ ባሎ፣ እና ዳርሰል ግራሃም የተባሉትን የሞንትጎመሪ ካውንቲ ላይብራሪስ ዳይሬክተር በወቅቱ ነፓነሊስትነት ቀርበው የሞንትጎመሪ ካውንቲ ለነሱ ያለውን ትርጉም በመተንተን እና ታሪኩን እና የወደፊት እቅዳችንንም በተመለከተ በክብር ለማሰብ የምናደርገውን ጥረት በተመለከተም ማብራሪያ በመስጠታቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ።
የሞንትጎመሪ ካውንቲ የትራንስፖርት መምሪያ ለ ዩ ኤስ 29 አውራ ጎዳና የፈጣን አውቶቡስ ትራንሲት 2ኛ ደረጃ ፕሮጀክትን በተመለከተ ጥቅምት 7 ከ6-8 ፒ ኤም በሞንትጎመሪ ብሌር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የህዝብ ውይይት ያካሂዳል። ይህ ፕሮጀክት ከስላይጎ ክሪክ ፓርክዌይ እስከ ቴክ ሮድ ባለው መንገድ ላይ ለአውቶቡስ ብቻ የተወሰነ መንገድ /lane/ በመገንባት አሁን ያለውን የዩ ኤስ 29 ፍላሽ ፈጣን የትራንዚት አገልግሎት እንደሚያሻሽለው ይጠበቃል። የመንገድ ትራንስፖርት መምሪያው የፕሮጀክቱን ቅድመደዛይን የሚያቀርብ ሲሆን የመምሪያው ሰራተኞችም የተለያዩ ጥያቄዎችን በመመለስ እና ዲዛይኑንም በተመለከተ ውይይት ያቀርባሉ። ስለፕሮጀክቱ የበለጠ ለማወቅ እዚህ ይጫኑ።
የኔ ቢሮ ከፓይክ ዲስትሪክት ጥምረት ጋር በመቀናጀት በዋይት ፍሊንት ፕላዛ የጽዳት ዘመቻ አካሂደን ነበር። በጽዳት ዘመቻው እገዛ በማድረግ ለተባበሩን በጎ አድራጊዎች እና የማህበረሰብ አባላት ምስጋና እናቀርባለን። ፓይክ ዲስትሪክት የሞንትጎመሪ ካውንቲ ዋና አካል በመሆኑ ይህ አካባቢ ከአመት አመት እየተሻሻለ አና እየተቀየረ መሄዱን ማየት አስደሳች ነው።
በሎንግ ብራንች ፌስቲቫል ከጎረቤቶቼ እና ከጓደኞቼ ጋር በመገኘት እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ምግብ፣ ዳንስ እና የመድረክ ሙዚቃ ለማጣጣም ችለናል። በፌስቲቫሉ ላይ በሎንግ ብራንች አንጸባራቂ የማህበረሰብ አባላት የቀረቡ የተለያዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች የተስተናገዱ ሲሆን፣ የአካባቢ እደጥበብ ባለሞያዎች እንዲሁም ኤል ጎልፎ፣ ኤል ጋቪላን፣ ላካሲታ፣ ማንሳ ኩንዳ፣ ላቭ ኤንድ ፍሎር ዳቦ መጋገሪያ እና ኮማ ቡና የተባሉ ሬስቶራንቶች እና ምግብ ሻጮችም የተካፈሉበት ነበር። በጣም ቆንጆ የሆኑ ፊኛዎችን ያቀረቡልንን ሮዛና የአበባ መሽጫም ሳናመሰግን አናልፍም!
አዲሱ የታኮማ ፓርክ ላይብራሪ አሁን ክፍት ነው! ይህ ፕሮጀክት ከታሰበ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ተጠናቆ እና ብዛት ያላቸው የማህበረሰብ አባሎቻችን እና የመንግስት አካል አጋሮቻችን በተሳተፉበት ሁላችንም ተገናኝተን ይህን ውብ ተቋም ሪባን ቆርጠን ስንመርቅ እጅግ ደስታ ይሰማናል። ላይብረሬው በታኮማ ፓርክ የሚኖሩ ሰዎችን ህይወት ከማሻሻሉም በላይ የማህበረሰብ አባላቱ እንዲገናኙ እና አብረው እንዲሆኑ የሚያግዝ ተቋም ነው። በተጨማሪም በላይብረሪው የሚገኘው የኮምፒዩተር ማእከል ሁሉም ተጠቃሚ የዲጂታል ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም ወይንም የዲጂታል አለም ተሳታፊ እንዲሆን ይረዳል። በአዲሱ አድራሻው (101 Philadelphia Ave.) ከሰኞ እስከ ሃሙስ ከ10 ኤ ኤም እስከ 8 ፒ ኤም ወይንም ከአርብ እስከ እሁድ ከ12 ፒ ኤም እስከ 6 ፒ ኤም በመምጣት በዚህ የማህበረሰብ መገልገያ ተቋም ተጠቃሚ እንድትሆኑ እንጋብዛለን።
በዚህ ወር ራስ ማጥፋትን ለመከላከል ግንዛቤ መፍጠር ጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት እንሞክራለን። ብዙዎቻችን ስቃያችንን በዝምታ እይዛለን። ነገር ግን አብረን በመቆም፣ ዝምታንም በመስበር እና እርስ በርስ መተሳሰብን በማሳደግ ለሁላችንም ደህንነቱ የተጠበቀ እና አጋዥ የሆነ ማህበረሰብ መፍጠር እንችላለን።
እርስዎ ወይንም ሌላ የሚያውቁት በዚህ ጉዳይ የተቸገረ ሰው ካለ እገዛ ማግኘት ይቻላል።
ትሪ ኦፍ ሆፕ በአቻዎች የሚመራ / peer-led/፤ በዋነኛነት ደግሞ በበጎ ፈቃደኞች የሚተዳደር እና በማገገም ላይ ላሉ ማህበረሰቦች እገዛ የሚያደርግ ማህበር ነው። ትሪ ኦፍ ሆፕ በመጠለያ ጣቢያዎች እና በህክምና ማእከሎች ውስጥ የሚገኙ የአቻ ቡድኖች እንዲሁም በሺዎች ለሚቆጠሩ በቅድመ ማገገገም ላይ ላሉ ግለሰቦች የአንድ ለ አንድ እገዛ ይሰጣል። አላማው ሰዎችን ለመገንዘብ በሚያስችል መልኩ ባሉበት ቦታ በማግኘት እና ስለሁኔታቸው በመገንዘብ የኑሮ መሰረታቸውን እንዲገነቡ እና የማገገም ጉዞአቸውንም እንዲያጠናክሩ ማገዝ ነው።
በበጋው ወራት ትሪ ኦፍ ሆፕ በማገገም ላይ ያሉ ወጣቶችን በማገዝ ላይ ያተኮረ አዲስ ክለብ ሃውስ ከፍቷል። ትሪ ኦፍ ሆፕ የግለሰቦችን ብቃት በማሳደግ በማገገም ሂደት ላይ ሊኖሩ የሚችሉ የመገለል ሁኔታዎችንም ለማስወገድ ተግቶ ይሰራል። በስራው ለመሳተፍ እና ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እዚህ ይጫኑ።
