ውድ ጓደኞቼ፣
እኛ በሞንትጎመሪ ካውንቲ የምንገኝ በአሁኑ ሰአት በነዋሪዎቻችን ህልውና ላይ አደጋ እያመጣ ያለውን የፕሬዚደንት ትራምፕን በጥላቻ የተሞላ አጀንዳ እና በግዴለሽነት የመንግስትን ስራ የመዝጋት እርምጃ አጥብቀን በመቃወም እንቆማለን። ይህ የመንግስት መዘጋት በያንዳንዳችንን ህይወት ላይ በሁሉም መልኩ ተጽእኖ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩትን በሞንትጎመሪ ካውንቲ የሚኖሩ የፌደራል ተቀጣሪ ሰራተኞችን በቀጥታ የሚፈታተን እንዲሁም ህልውናቸው በሴፍቲ ኔት እርዳታ ላይ የተመሰረተ ብዙ ነዋሪዎቻችንንም የሚጎዳ ነው።
ባለፈው ሳምንት የኮንግረስ አባል ከሆኑት ከኤፕሪል ደላኔይ እና ከዴሞክራቲክ የሴቶች ተወካዮች ስብስብ /Congressional Democratic Women’s Caucus/ ጋር በመሆን የአፕካውንቲ ሪጅናል ሰርቪስ ማእከልን ተዘዋውረን የጎበኘን ሲሆን በዛውም በአካባቢ ደረጃ አብረን በመስራት እንዴት ነዋሪዎቻችንን በጣም ጠቃሚ ከሆኑ የጤና አና የማህበራዊ እገዛ አገልግሎቶች፣ የስራ ቅጥር እገዛ እንዲሁም ከህብረተሰብ ጤና ፕሮግራሞች ጋር ማገናኘት እንደምንችል አንድ በአንድ እና በቀጥታ ተወያይተናል።
የአሁኑ የፌዴራል መንግስት አስተዳደር ከጀመረ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ስናደርግ እንደቆየነው አሁንም ከስቴት እና ከፌዴራል የስራ ሃላፊዎች ጋር አብረን በመሆን የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ መስራታችንን እና የትራምፕ አስተዳደር በወሰዳቸው እርምጃዎች ምክንያት ተጽእኖ ለደረሰባቸውም ነዋሪዎች እና ቤተሰቦችም መጠነ ሰፊ የሆኑ እገዛዎችን ማድረጋችንን እንደምንቀጥል ለማረጋገጥ እንወዳለን።
ከኋይት ሃውስ ለሚደርስባቸው ጫና እጅ ሳይሰጡ ቁጥራቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ነዋሪዎቻችን በመቆርቆር የሚቆሙትን በዋሽንግተን የሚገኙ የፌዴራል መንግስት አጋሮቻቻንንም በዚሁ አጋጣሚ ለማመስገን እወዳለሁ። እርስ በርሳችን በመደጋገፍ፤ ጎረቤቶቻችንም በማገዝ ሃገራችን ቀና ብላ እንድትቀጥል በጠንካራ ሁኔታ እየሰሩ ላሉ የመንግስት ሰራተኞችም ድጋፋችንን መስጠት መቀጠል ይኖርብናል።
እንደተለመደው ምንም አይነት ጥያቄ ካላችሁ እና እገዛ ከፈለጋችሁ በነጻነት ወደ ቢሮዬ መምጣት/ማግኘት እና መነጋገር ትችላላችሁ።
ከሰላምታ ጋር፣
ኬት ስቴዋርት
የካውንስሉ ፕሬዚደንት
የሜሪላንድ ስቴት ገዥ ዌስ ሙር በፌዴራል መንግስት ስራ በመዘጋቱ ምክንያት ተጽእኖ የደረሰባቸውን የሜሪላንድ ነዋሪዎች ሊያግዙ የሚችሉ የተለያዩ ሃብቶች እና መረጃዎችን አስታውቀዋል። በመሆኑም ከታች ተዘረዘሩት ርእሶች ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለማግኘት የ the State of Maryland ድረገጽን መጎብኘት ይቻላል።
የፌዴራል ተቀጣሪዎች ወቅታዊ መረጃ ለማግኘት የዩ ኤስ የሰራተኞች ቅጥር አስተዳደርን ድረገጽ - the U.S. Office of Personnel Management - መጎብኘት ይችላሉ። የፌዴራል አጋሮቻችን የሚከተሉትን ለፌዴራል መንግስት ተቀጣሪዎች የሚሆኑ ሃብቶችን አጋርተውናል። ይጎብኟቸው።
የሞንትጎመሪ ካውንቲ መንግስት አስተዳደር ከማህበረሰብ አጋሮች ጋር በመሆን በመንግስት መዘጋት ምክንያት የደረሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል። ተጽእኖ የደረሰባቸው ነዋሪዎች የካውንስሉን የአገልግሎት እና እገዛ ትብብር ድረገጽ - United in Service and Support community resources page -/ መጎብኘት ወይንም ደግሞ በ 311 ስልክ በመደወል ከምግብ፣ ከመኖሪያ ቤት፣ ከአእምሮ ጤና እንዲሁም ከስራ አጥነት ካሳ ጋር የተያያዙ እገዛዎችን በተመለከተ ወቅታዊ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።
ባለፈው መስከረም መጨረሻ አካባቢ በመኪና ተገጭተው ህይወታቸው ባለፈው ሁለት የእግረኞች ጉዳይ እጅግ በጣም ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶናል። አንደኛው ግለሰብ በኬንሲንግተን ውስጥ በዩኒቨርሲቲ ቡሌቫርድ ዌስት ጎዳና በ3600 ብሎክ አካባቢ ለማቋረጥ ሲሞክር የተገደለው የ16 አመት እድሜ ያለው ጄምስ ኤቨርት አንደርሰን ሲሁን ሁለተኛዋ ተጎጂ ደግሞ በዊተን በቪርስ ሚል መንገድ ላይ በገጭቶ ማምለጥ ምክንያት ህይወቷን ያጣችው የ52 አመቷ የኒው ካሮልተን ነዋሪ የሆነችው ጋንጃ ፕራጃፓቲ ነች። ህይወታቸው እንደዚህ በሚያሳዝን ሁኔታ በአጭር ለተቀጠፈው ለነዚህ ሁለት ግለሰቦች ቤተሰቦች እና የቅርብ ወዳጆች የተሰማኝን ጥልቅ የሆነ ሃዘን ለመግለጽ እወዳለሁ።
ከስቴት ተወካዮች ጋር ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርብ ምክክር ያደረኩ ሲሆን በተለይ በነዚህ አካባቢዎች የተጠናከረ የአሽከርካሪ የፍጥነት ቁጥጥር እንዲደረግ እና አስፈላጊ የሆኑ ሌሎችም አይነት የእግረኞችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች ከትራንስፖርት መምሪያ ጋር በመቀናጀት የሚተገበሩበትን ሁኔታም ተወያይተናል። በዚህ አጋጣሚም ሁሉም አሽከርካሪዎች ፍትነት ቀንሰው እንዲጓዙ እና የተቀመጡ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ምልክቶችንም እንዲያከብሩ እንዲሁም የእግረኞችን እና የብስክሌት ነጂዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት እየተጠነቀቁ እንዲያሽከረክሩ ለማስታወስ እወዳለሁ።
እኔ ወክዬ የተመረጥኩበት ዲስትሪክት ወደ ስራ፣ ወደ ትምህርት ወይንም ወደ ገበያ ለመሄድ በእግር፣ በብስክሌት ወይንም የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ ብዙ የማህበረሰብ አባላት ያሉበት እና በአጠቃላይም ብዙ እግረኞች የሚበዙበት ዲስትሪክት ነው። በመሆኑም የእግር ተጓዦች ደህንነት የኔም ሆነ አጠቃላይ የምክር ቤታችን ሁሌም በአንደኛ ደረጃ የምናስቀምጠው ጉዳይ ነው። የትራንስፖርት እና የአካባቢ ኮሚቴም በቅርቡ በፐርፕል ላይን የባቡር መንገድ ኮሪዶር ላይ የብስክሌተኞችን እና የእግረኞችን ሁኔታ ለማሻሻል በሚል ስብሰባ አካሂዶ ነበር። ዝርዝሩን ይህን - briefing about bicycle and pedestrian improvements along the Purple Line corridor - ማስፈንጠሪያ በመጫን ማየት ይቻላል። በመሆኑም መሰረተ ልማቶቻችንን እንደገና ደዛይን በምናደርግበት እና በምንገነባበት በማንኛውም ወቅት የምንቀርጻቸው የወደፊት ፕላኖች በሁሉም እድሜ እና ችሎታ ላይ የሚገኙ የእግር መንገደኞች እና ብስክሌተኞችን ደህንነት ማእከል ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል።.
በሞንትጎመሪ ካውንቲ ፓብሊክ ስኩልስ /MCPS/ ሰራተኞች የጀርባ ማጣራት ሂደት ላይ በጣም ግዙፍ መጓተት ውይንም ውዝፍ ስራ እንዳለ ያመለከተው እና የኤም ሲፒ ኤስን የጀርባ ጥናት ቢሮ አሰራር የገመገመው የዋና መቆጣጠሪያ ቢሮ ረፖርት መለቀቁን ተከትሎ እኔ በሊቀመንበርነት የምመራው የምክር ቤት የኦዲት ኮሚቴ በቅርቡ የክትትል ስብሰባ / oversight meeting / በማድረግ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፓብሊክ ስኩልስ ወቅጣዊ መረጃዎችን እንዲሰጥ አድርጓል።
የኤምሲፒኤስ አመራሮች ይህን ውዝፍ ስራ ለማቃለል እየተደረጉ ያሉ የተወሰኑ ስራዎችን በተመለከተ ተወያይተዋል። እነኚህ የጀርባ ማጣራት ስራዎች የተማሪዎቻችንን እና የትምህርት ቤቶቻችንን ሰራተኞች ደህንነት ለመጠበቅ በጣም ጠቃሚ በመሆናቸው ይህን በጣም አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ለማቃለል ስለተወሰዱ እርምጃዎች መነጋገር እና በዛውም አጠቃላይ የትምህርት ቤቱን ስርአት እና አጋሮችንም በማነጋገር ይህን ችግር ለመቅረፍ ምን መደረግ እንዳለበት እና በምን ያህል ጊዜም እርምጃዎቹ መጠናቀቅ እንደሚኖርባቸው መወያየት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። እኔና የስራ ባልደረቦቼ በየቀኑ ጉዳዩ ከሚያሳስባቸው ወላጆች ጥያቄ የሚቀርብልን ሲሆን እኔም አንድ ጉዳዩ እንደሚመለከተው ወላጅ ይህ ጉዳይ በጣም ያሳስበኛል። የኦዲት ኮሚቴው ከኤምሲፒ ኤስ ጋር ቀጣይ ስብሰባዎችን በመጪው የበልግ ወቅት የሚያደርግ ይሆናል።
የሞንትጎመሪ ካውንቲ የፖሊስ መምሪያ /MCPD/ ማህበረሰቦቻችንን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እንዲረዳ ታልሞ የተዘጋጀውን የ2025 የማህበረሰብ እምነት የዳሰሳ ጥናት በመሙላት እንዲሳተፉ ነዋሪዎችን ይጋብዛል። በረቂቅ ደምቡ ቁጥር 45 20 መሰረት ማህበረሰቡ ለህግ አስከባሪዎች አባላት ያለውን የአመኔታ ደረጃ መለካትን ጨምሮ በአጠቃላይ በፖሊስ እና በማበረሰቡ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመገምገም የፖሊስ መምሪያው በየአመቱ ስም በማይጠቀስበት መጠይቅ ነዋሪዎችንም የፖሊስ መኮንኖችንም የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ያካሂዳል። የዚህ ዳሰሳ ጥናት ውጤትም ከሌሎች ተፈላጊ መረጃዎች ጋር ተጠናቅሮ በ2026 መጀመሪያ አካባቢ በፖሊስ የአሃዝ መረጃ ረፖርት /Police Statistical Data Report/ ውስጥ ይታተማል። የዳሰሳ ፎርሙን ለመሙላት ከ1 እስከ 2 ደቂቃ ብቻ የሚፈጅ ሲሆን ፎርሙም በእንግሊዝኛ፣ በስፓኒሽ እና ቻይና ቋንቋዎች የተዘጋጀ ነው። የዳሰሳ ፎርሙን እዚህ ላይ በመጫን ዛሬውኑ ይሙሉ።
አዲስ የተመረጡትን የፓይክ ዲስትሪክት ጥምረት የቦርድ ፕሬዚደንት አንድሪው ሹልማን እና የአዲሱን የአመራር ቡድን አባላት እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ! ከሹልማን እና ከአዳዲስ መጪዎቹ የቦርድ አባላት ጋር አብሬ ለመስራት እና በኖርዝ ቤተዝዳ የሚገኘውን እና እያበበ ያለውን የፓይክ ዲስትሪክት ቀጣይ የልማት ሂደት ለማስቀጠል ያለንን ጉጉት ለመግለጽ እወዳለሁ።
ከካውንቲው ስራ አፈጻሚ ማርክ ኢልሪች፣ ከኤምሲፒኤስ የበላይ ተቆጣጣሪ ዶ/ር ቶማስ ቴይለር፣ ከኤች ኤች ኤስ/ ጤና መምሪያ/ ዳይሬክተር ዶ/ር ጄምስ ብሪጅስ እንዲሁም ከቅድመ መደበኛትምህርት ዝግጅት / Head Start/ ተከታታይ ህጻን ወላጅ ግሎሪያ ሙሲመንታ እና የላቲኖ ህጻናት እንክብካቤ ማህበር/ Latino Childcare Association/ ፕሬዚደንት አንቶኒዮ ሀርናንዴዝ ጋር አብሬ በመሆን n የ$10 ሚሊዮን የለጋ ህጻናት ቅድመ መደበኛ ትምህርት / early childhood education መዋእለ ነዋይ/ኢንቨስትመንትን ድጋፍ ሳበስር በጣም ኩራት ተሰምቶኝ ነበር። ይህ የገንዘብ ድጎማ አላማ ያደረገው በማህበረሰቦች ውስጥ የሚታዩ የአለመመጣጠን ጉድለቶችን በማስተካከል በተለይ በቂ አገልግሎት ለማይደርሳቸው ማህበረሰቦች የሚገባቸውን አገልግሎቶች ከሌላው እኩል እንዲያገኙ ለማስቻል ነበር። ጠንካራ የሆነ፣ ችግሮችን የሚቋቋም የቅድመ እንክብካቤ እና የትምህርት ስነምህዳርን በመፍጠር የሚታዩ ክፍተቶች ከማደጋቸው በፊት በእንጭጩ ለመቅጨት እና ለማስተካከል እየሰራን እንገኛለን። በአጠቃላይ ዋና አላማችን ለሁሉም ነዋሪ በበለጠ ሁኔታ እኩል እና ፍትሃዊ እድልን የሚያጎናጽፍ እና የበለጸገ የሞንትጎመሪ ካውንቲን መገምባት ነው።
ባለፈው ሳምንት ካውንስሉ በኮራዞን ፎክሎሪኮ የዳንስ ቡድን በቀረበ ልዩ ባህላዊ የዳንስ ዝግጅት ታጅቦ 12ኛውን አመታዊ የሂስፓኒክ ቅርስ መታሰቢያ ወር አክብሯል። የዚህ አመት መታሰቢያ አከባበር ዋና ጭብጥ “በግስጋሴ ላይ ያለ የታሪክ ቅርስ፣ ያለፈውን ማወደስ፤ የወደፊቱን ማነሣሣት” የሚል ሃረግ የያዘ ሲሆን ይህም መመሪያ ዝም ብሎ ቃላት ብቻ ሳይሆን በካውንቲያችን ቀን ተቀን የምናየው እውነታ ነጸብራቅ ነው። በዚህም አመት የመመሪያው መገለጫ የሆኑትን እና ከነሱ በፊት የተፈጠሩ ታሪክ ሰሪዎች በጣሉት መሰረት ላይ በመመስረት ለሁላችንም የወደፊት ህይወት መሻሻል ትርጉም ያለው ስራ እየሰሩ ያሉትን እና የማህበረሰባችን አባላት የሆኑትን ጀፈርሰን ረየስ፤ ገብርየላ ራሞ እና ጉስታቮ ቶረስ እውቅና ሰጥተናል። በደስታ የተሞላ የሂስፓኒሽ ቅርስ መታሰቢያ ወር እንድታሳልፉ እንመኛለን!
በዳውንታውን ሲልቨር ስፕሪንግ በተካሄደው የሶስተኛ አመታዊ የባኬትስ አንድ ቢትስ ብሎክ ፓርቲ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ችለናል! ይህ ለኔ በአመቱ ከሚካሄዱ እና ከምወዳቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ ነው ማለት እችላለሁ። በዝግጅቱም የመካከለኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከትምህርት ቀደም ብለው ተለቀው ለነሱ የሚሆኑ ብዙ አዝናኝ እንቅስቃሴዎችን የሚዩዩበት እና የሚደሰቱበት ዝግጅት ነው። ብዙ ተማሪዎች እና ወላጆችም በዚህ ዝግጅት በመካፈል በመገኘታቸው አስደስቶኛል። በሚቀጥለው አመትም በሲልቨር ስፕሪንግ ረጅናል የአገልግሎት መስጫ ማእከል እንዳምናዘጋጀው በጉጉት እጠብቃለሁ! ይህ ዝግጅት እንዲሳካ አስተዋጾ ላደረጉ ብዙ ቁጥር ያላቸው አጋሮቻችንም ታላቅ ምስጋና ማቅረብ እሻለሁ። እነሱም፤ የመዝናኛ ፕሮግራሞች መምሪያ፣ የማህበረሰብ የህዝብ ተቋማት አገልግሎት /CUPF/፣፣የጤና ጥበቃ መስሪያ ቤት /DHHS/፣ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ፖሊስ መምሪያ /MCPD/፣ የዋነኛው ሲልቨር ስፕሪንግ የንግድ ምክር ቤት፣ ዩናይትድ ቴራፑቲክስ፣ የሲልቨር ስፕሪንግ የወጣቶች ማእከል /YMCA/፣ ክሪኤት አርትስ፣ ሬዲዮ ዋን፣ አማዞን ፍሬሽ፣ እና የፒተርሰን ኮምፓኒስ ይጠቀሳሉ።
የተንቀሳቃሽ የህክምና እንክብካቤ ኩባንያ ወይንም ሞባይልሜድ /"MobileMed"/ Mobile Medical Care, Inc., ኢንሹራንስ ለሌላቸው፣ በዝቅተኛ ገቢ ኢንሱራንስ የሚጠቀሙ እና ሜዲኬር/ሜዲኬድ ኢንሹራንስ ለገቡ የሞንትጎመሪ ካውንቲ ነዋሪዎች የተሟላ መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ በፌዴራል ደረጃ ብቃቱ የተረጋገጠ ማእከል ነው። በተጨማሪም ሞባይልሜድ በሞንትጎመሪ ካውንቲ ካሉ በጣም ግዙፍ የሆኑ በሞንትጎመሪ ኬርስ ፕሮግራም አማካኝነት የሴፍቲ ኔት አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች አንዱ ነው። አላማቸውም መሰረታዊ ጥቅማጥቅሞችን ለማግኘት ትልቅ ተግዳሮቶች የሚገጥሟቸውን እና ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኙ ነዋሪዎችን ጤና ማሻሻል ነው። እያንዳንዱ የመሰረታዊ የጤና ታካሚ ለጭንቀት፣ ፍርሃት/ አንግዛይቲ/ እና ፒቲኤስ ዲ የተባሉ የአእምሮ በሽታዎች እንዳሉበት እና እንደኤለበት ቅድመ ምርመራ እንዲያደርግ ይደረጋል። ካስፈለገ እና ምርጫቸው ከሆነ ታካሚዎች የፍቃድ ሰርተፊኬት ወዳለው እና ሁለት ቋንቋዎችን ወደሚናገር የጤና አገልግሎት ባለሞያ ለህክምና፣ ለመድሃሚት አወሳሰድ ክትትል፣ ለስነልቦናዊ ጤና ምርመራ ወይንም ደግሞ ከዛም ወደበለጠ አገልግሎት ወደሚሰጥበት ተቋም ሊመራ ይችላል። ሞቢልሜድ በጀርመንታውን፣ በሮክቪል፣ በአስፐን ሂል፤ እና በሲልበር ስፖንግ አካባቢ ክሊኒኮች አሉት። የስነባህሪ ጤና አገልግሎት በአካል በመቅረብም ሆነ በስልክ/ቴሌሄልዝ ሊሰጥ ይችላል። የበለጠ ለመረዳት www.mobilemedicalcare.org የሚለውን ይጫኑ ወይንም በ301-493-2400 ስልክ ይደውሉ።
በእድሜ የገፉ ሰዎች በአካላዊ፣ በስነአእምሯዊ እንዲሁም በማህበራዊ ኑሯአቸው ጤናማ የሆነ እና በእንቅስቃሴ የተሞላ ህይወትን ለመግፋት እንዲችሉ ለማድረግ ከሚደረጉ አለም አቀፋዊ ጥረቶች መሃል አንዱ የሆነውን አክቲቭ ኤጂንግ /Acrive Aging/ ሳምንት ሞንትጎመሪ ካውንቲ ከሰኞ ጥቅምት 6 እስከ ጥቅምት 12 ሞንትጎመሪ ካውንቲ ያከብራል። በዚሁ ሳምንት ውስጥ እድሜያቸው 50 እና ከዛም በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች በነጻ የሚቀርቡትን የተለያዩ ብዛት ያላቸው ፕሮግራሞች፣ ዝግጅቶች እና እንቅስቃሴዎች መጥተው ይመልከቱ ። የሚካሄዱ ዝግጅቶችን በተመለከተ የተዘጋጀውን ሙሉውን ፕሮግራም ይህን የካውንቲውን ድረ ገጽ በመጫን ያገኛሉ።
